ሸማቹን እና ነጋዴውን ተጠቃሚ የሚያደርግ የንግድ ስርዓት ለማስፈን እየተሰራ ነው:- አቶ ገብረመስቀል ጫላ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር

ሸማቹን እና ነጋዴውን ተጠቃሚ የሚያደርግ የንግድ ስርዓት ለማስፈን እየተሰራ ነው:- አቶ ገብረመስቀል ጫላ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ================== አዲስ አበባ 04/07/2016(የንቀትሚ) የሸማቹን እና የነጋዴውን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ዘመናዊ የንግድ ስርዓት ለማስፈን እየተሰራ ነው ሲሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ተናገሩ፡፡ ለዘመናት በተለያዩ ስርዓቶች ውስጥ ያለፈውና ኋላቀር የሆነውን የኢትዮጵያ የንግድ ህግ ወቅቱ በሚጠይቀው እና ዓለም አቀፋዊ ንግድን ማስተናገድ በሚችል መልኩ መቀየሩን የገለጹት ሚኒስትሩ በሀገሪቱ ካሉት ነጋዴዎች ውስጥ 89 በመቶ የሚሆኑት ባሉበት ቦታ ሆነው የንግድ አገልግሎቶችን ማግኘት ችለዋል ብለዋል፡፡ እንደሚኒስትሩ ገለጻ በንግድ ስርዓቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ንረት፣ ህገ-ወጥነት እና መሰል ችግሮችን ለማስወገድ ዋነኛው ስልት የንግድ ስርዓቱን እና የምርት አቅርቦት ሰንሰለቱን ዲጂታል ማድረግ ነው። በዚህም በነዳጅ አቅርቦትና ግብይት ላይ ተግባራዊ የተደረገው ዲጂታላይዜሽን ውጤታማ በመሆኑ በሌሎችም የተመረጡ የግብርና ምርቶች ላይ ለመተግበር ጥናቶች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ የሀገር ውስጥም ሆነ የወጪ ንግዱን እየፈተነው ያለውን ኮንትሮባንድ እና ህገ-ወጥነት በማስቀረት ነገዴውን እና ሸማቹን ተጠቃሚ የሚያደርግ የንግድ እና የግብይት ስርዓትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ሸማቹ ህብረተሰብ እና የሸማቾች መብት ጥበቃ ማህበር ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር መዋቅር ጎን ሆኖ አይተኬ ሚናውን መወጣት አለበት ሲሉም ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

Share this Post