ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ ነዳጅ ማደያዎች ላይ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል - የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን

ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ ነዳጅ ማደያዎች ላይ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል - የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አዲስ አበባ3/09/2016(ንቀትሚ) ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ ነዳጅ ማደያዎች ላይ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል አዋጅ መዘጋጀቱን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታወቀ። አንዳንድ ነዳጅ ማደያዎች ሰው ሰራሽ ችግር የመፍጠር አዝማሚያና በሙሉ አቅማቸው ያለመስራት ችግር በመፍጠር ደንበኞች እንዲጉላሉ ሲያደርጉ ይስተዋላል። በነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ እያለ እንደሌለ ማስመሰል፣ የነዳጅ ግብይትን በጥሬ ገንዘብ መሸጥ፣ ነዳጅን በተለያዩ ስፍራዎች ደብቆ ማስቀመጥ፣ በነዳጅ ማደያዎች ከፍተኛ ወረፋ እንዲኖር ማድረግና በነዳጅ ኮንትሮባንድ ንግድ ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ። የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሰሃረላ አብዱላሂ በኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ የነዳጅ ማደያዎች ላይ ከማሸግ የዘለለ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሕጋዊ አሰራር እንዳልነበር ለኢዜአ ገልጸዋል። ከችግሩ አሳሳቢነት አኳያም ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ማደያዎቹን ከማሸግ ያለፈ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችል አዋጅ መዘጋጀቱን አመልክተዋል። በአዋጁ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት በሚፈጥሩ ሕገ ወጦች ላይ እስራትና የገንዘብ ቅጣት እርምጃ መውሰድ የሚያስችሉ አንቀጾች መካተታቸውን ጠቁመዋል። በአዋጁ ላይ ከነዳጅ ኩባንያዎች፣ ከፈሳሽ ጭነት አሽከርካሪ ማህበራትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ግብዓት መሰብሰብ መቻሉን ነው ዋና ዳይሬክተሯ የገለጹት። አዋጁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን ተከትሎ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ጠቁመዋል። በሌላ በኩል ባለስልጣኑ በዘርፉ ያለውን ሕገ-ወጥነት ለመከላከል ከአምስት ወር በፊት አዳዲስ የነዳጅ ማደያ ፈቃድ እንዳይሰጥ ክልከላ ማድረጉን አስታውሰዋል። ክልከላው የተደረገው ለነዳጅ ማደያ ግንባታ ራሱን የቻለ ደረጃና መስፈርት ባለመውጣቱ ነው ብለዋል፡፡ ባለስልጣኑ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢኒስቲትዩት ጋር በመሆን ለነዳጅ ማደያ ግንባታ የሚያስፈልግ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የጥራት መስፈርት ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል። የነዳጅ ማደያ ፈቃድ የመስጠት ስራው በድጋሚ ሲጀመር በወጣው መስፈርት መሰረት ማደያዎች ፈቃድ እንደሚሰጣቸውና የሚገነቡበት ስፍራ የቦታ ሽፋን ገደብ እንደሚቀመጥም ነው ያብራሩት። የነዳጅ ማደያዎች በጥራት መስፈርቱ አማካኝነት ማደያ የመገንባት ፍላጎታቸውን አስቀድመው የማሳወቅ ግዴታ እንዳለባቸው ጠቅሰዋል። የዚህ አይነት አሰራር መዘርጋቱ ሕገ ወጥነትን ከመከላከልና ሕጋዊ አካሄድን ከማጠናከር አኳያ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ነው ዋና ዳይሬክተሯ የተናገሩት።

Share this Post