ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊና የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር እየሰራች ነው - አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊና የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር እየሰራች ነው - አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ================== አዲስ አበባ 19/09/ 2016(ንቀትሚ) ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊና የንግድ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተናገሩ። ኢትዮ-ፓኪስታን የቢዝነስ ምክክር መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል። በምክክር መድረኩ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ፣ በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር፣ የፓኪስታን የንግድ ልማት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሞሃመድ ዙቤር ሞቲዋላ ጨምሮ ከፍተኛ የቢዝነስ ልዑካን ቡድን ተገኝተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊና የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል። በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካራቺ በረራ ከጀመረ በኋላ ፓኪስታንን ከአፍሪካ ብሎም ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት እየተጠናከረ መሄዱን ገልፀው በቀጣይ ሁለቱ ሀገራት በዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዘርፎች ያላቸው ግንኙነት ይበልጥ በሚጠናከርባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል። የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት የገለጹት ሚኒስትሩ በዚህም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን በማንሳት፤ ለዚሁ ማሳያ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አንዱ መሆኑን አብራርተዋል። ኢትዮጵያ ከፓኪስታን መልካም ተሞክሮ ባካበተችባቸው የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ፋርማሲዩቲካልና ሌሎች ዘርፎች በጋራ መሥራት እንደምትፈልግ ገልጸው የቢዝነስ ልዑካን ቡድኑም በኢትዮጵያ በዘርፉ ኢንቨስት የሚያደርጉበት ሰፊ አማራጭ እንዳለ ገልፀዋል። የፓኪስታን የንግድ ልማት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሞሃመድ ዙቤር ሞቲዋላ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ማድረጓ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ ትሠራለች ብለዋል። በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከረዥም ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ፓኪስታን ካራቺ በረራ መጀመሩ ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ ትስስር ለማጠናከር ቁልፍ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል ሲል ኢዚያ ዘግቧል።

Share this Post