“ያለ ምርት ጥራት የገበያ ውድድር አይታሰብም”-ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

“ያለ ምርት ጥራት የገበያ ውድድር አይታሰብም”-ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) AMN-ነሐሴ 22/2016 ዓ.ም በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተዘጋጀውና አራተኛ ቀኑን የያዘው “የኢትዮጵያን ይግዙ” የንግድ ሳምንት ኤግዚቪሽንና ባዛር አካል የሆነው በምርት ጥራት ዙሪያ የሚደረገው የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡ ውይይቱን አስመልክተው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶክተር ካሳሁን ጎፌ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ያለ ምርት ጥራት የገበያ ውድድር አይታሰብም ብለዋል:: ጥራት የሁሉም ቋጠሮ መፍቻና የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ንግድ በማስተሳሰር አይተኬ ሚና ያለው ነው ያሉት ሚኒስትሩ ዋጋ የሚወሰነውና መወዳደር የሚቻለው በተመረተው ምርት ጥራት ልክ መሆኑን ገልጸዋል:: “የኢትዮጵያን ይግዙ ስንል ከወጪ የሚገቡ ምርቶችን መተካት ብሎም በጥራት እየተመረተ ያለውን የሀገራችንን ምርት ለመላው ዓለም ማስተዋወቅ ነው” ሲሉም አስፍረዋል:: የምርት ጥራትን ለማስጠበቅና ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ የጥራት ማዕከል የሚያደርጋት የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት ተገንበቶ በቅርቡ እንደሚመረቅ አስታውቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ሀገራት ምርት እያቀረበች መሆኑን የገለጹ ሲሆን የኢትዮጵያን ምርት መግዛት መልመድና ባህል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል:: ኢትዮጵያ ያላትን የወጭ ንግድ ዕምቅ አቅም የሚያስተዋውቅ ቋሚ ኤግዚቢሽን ማዕከል ተገንብቶ መመረቁና ለጎብኝዎች ክፍት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

Share this Post