ኦን-ላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ሐምሌ1/2014 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ይጀመራል፣

ኦን-ላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ሐምሌ1/2014 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ይጀመራል፣ ≡========================================== እ.ኢ.አ በ2018/19 የሀገራትን የንግድ ስራ አመችነት አስመልክቶ የአለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ የንግድ ስራ ለመጀመር ባላት አመችነት (Ease of starting a Business) ከ190 ሀገራት 168ኛ፣ የንግድ ስራ ለመስራት ባላት አመችነት (Ease of doing Business) 159ኛ ደረጃ ላይ ተገኝታለች፡፡ የንግድ ስራ አለም አቀፋዊ ነው።በተለይም አሁን በደረስንበት ዘመነ ግሎባላይዜሽን ሀገራችን ከዚህ ቀደም ስትጠቀምበት በነበረው የንግድ ስርዓት ከዓለም ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ ሆና መቀጠል አትችልም፡፡ በዚህም የተነሳ ባለፉት 5 ዓመታት የሀገሪቱን የንግድ ስርዓት የአለም አቀፉ የንግድ ሂደት ከደረሰበት ደረጃ ጋር የሚተካከል ለማድረግ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል በመሰራት ላይም ናቸው፡፡ ቀደም ሲል በንግድ ሚኒስቴር፣ ሲቀጥልም በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አሁን ደግሞ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ስራን ቀላል ሳቢ፣ ምቹና ዘመናዊ ለማድረግ በርካታ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥም የንግድ ስራ ለመጀመርም ሆነ የንግድ ስራ ለመስራት ሀገራችን የነበራትን አመችነት/ Ease of starting business and Ease of doing business / ለማሻሻል የተሰሩ የሪፎርም ስራዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህም የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎትን ለማግኘት ይወስድ የነበረውን ጊዜ፣ ወጪና እንግልት በመቀነስ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ሀገራችን ለንግድና ኢንቨስትመንት ያላትን ተመራጭነት ለመጨመር ኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ተዘርግቷል፡፡ ይህ ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ጥር/2013 ዓ.ም ይፋ ተደርጎ ሙሉ በሙሉም ባይሆንም በከፈል ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በ2014 በጀት ዓመት 9 ወራትም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ16,541 ደንበኞች በኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልገሎት ተሰጥቷል፡፡ ይህ አፈጻጸም የእቅዱን 67 በመቶ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 10,813 የሚሆነው በፌደራል ደረጃ የተሠጠ ነው፡፡ ኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ከሐምሌ1/2014 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚደረግ የንግድ ሥርዓትና ላይሰንሲንግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ ተናግረዋል፡፡ ይህንን ውጥን እውን ለማድረግ እንዲቻል ብዙ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራታቸውንም የሚኒስቴር መ/ቤቱ የ9 ወራት ሪፖርት ያመለክታል፡፡ በ9 ወራቱ ውስጥ የኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት እና የተሻሻለውን የንግድ ሕግ ተግባራዊ ለማድረግ ከክልል እስከ ወረዳ ለሚገኙ 1,436 የንግድ ዘርፍ አመራርና ፈጻሚዎች በ7 ዙሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ በተመሳሳይ የአማራና የሲዳማ ክልሎች በኮምፒዩተር ላቦራቶሪ የተደገፈ የቴክኒክ ስልጠና እንዲሰጥላቸው በጠየቁት መሠረት ለ 136 ባለሙያዎች በተግባር የተደገፈ ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ ካሉት 1,134 የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች መካከል 1,082 (95.4%) ጣቢያዎች በወረዳ ኔት በማስተሳሰር አገልግሎቱን ከአንድ መረጃ ቋት እንዲያገኙ ተደርጓል። ቀሪዎቹ 52 ጣቢያዎችም እስከ ሰኔ/2014 ዓ.ም ወደ ወረዳ ኔታ እንዲገቡ ከክልሎች ጋር መግባባት ላይ ተደርሰል፡፡ ደንበኞች ለሚፈልጉት አገልግሎት አጭር የጽሁፍ መረጃ የሚያገኙበት መስመር (SMS) ቁጥር 872 መዘጋጀቱም አገልግሎቱን ከሐምሌ/2014 ጀምሮ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ለማዘመን ለተያዘው እቅድ ስኬታማነት ከተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ የዚህ ስርዓት መዘርጋት ሀገራችን በአለም አቀፍ ደረጃ የሀገራት የንግድ ስራ አመችነት መስፈርቶች መሰረት ያለችበትን ዝቅተኛ ደረጃ በማሻሻል በንግድና ኢንቨስትመንት ተመራጭነቷን ከማሳደጉም በተጨማሪ ወደ ንግድ ስራ ለሚገቡ እና በንግድ ስራ ውስጥ ላሉ የንግድ ማህበረሰቦች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የንግድ ስራን ያበረታታል፡፡ አሰራሩ ከንክኪ ነፃ በመሆኑ ሙስናን ያስቀራል፣ ጊዜና ወጪን በመቆጠብና እንግልትን በማስቀረት የደንበኞችን እርካታ ያሳድጋል፣ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትንም ያሳድጋል፡፡

Share this Post