ሴቶች የማህበረሰቡ ግማሽ አካል እንደመሆናቸው መጠን በእያንዳንዱ ማህበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ እኩል ተሳታፊ፣ ተወዳዳሪና ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ መንግስት የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡ የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ሴቶች በሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው፤ ተቋማዊና መዋቅራዊ አሰራሮችን ለመዘርጋት በር ከፍቷል፡፡
የሴቶችን እኩል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚደነግገው አንቀጽ 35 የስራ ቅጥርንና የመሬት ባለቤትነትን ጨምሮ በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል መብት እንዳላቸው በሰፊው ያትታል፡፡ መንግስት የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲያድግ በርካታ ስራዎችን በመስራቱ በየዘርፉ የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ከፍተኛ እድገት አሳይቷል።
ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም ህገ-መንግስቱ ለሴቶች የሰጠውን እድል ወደ ተግባር በመቀየር ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሴቶችና ወጣቶችን በንግድ ዘርፍ ተጠቃሚና ተሳታፊ ለማድረግ እየሰራ ሲሆን ከብሄራዊ የጥራት መሰረት ልማት ማሻሻያ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የሴቶች፣የወጣቶች እና የኢንተርፕራይዞችን አቅም የመገንባት ስራዎች እየተሰሩ መሆን በሚኒሰቴር መ/ቤቱ የወጣቶች ጉዳይ ቡድን መሪ አቶ ታደለ አስማረ ገልጸዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ድጋፍ የሴቶች አመራር/ Weman leadership/ እና የስርዓተ-ፆታ አካታችነት / Gender mainstreaming/ ስልጠና ማንዋሎች ተዘጋጅተው ደረጃውን በጠበቀ የህትመት ጥራት ታትሞ መሰራጨቱንም ቡድን መሪው ጠቅሰዋል፡፡ ብሄራዊ የጥራት መሰረት ልማት ማሻሻያ ፕሮጀክት በስራ ፈጠራ /Inovation/ እና በስራ እድል ፈጠራ /job opportunity/ ሴቶችን ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ለማድረግ ድጋፍ ባደረገባቸው የጨርቃጨርቅ፣ የግብርና ማፍቀነባበሪያ እና የቆዳ ውጤት አምራች ድርጅቶች ላይ ጉብኝትና የልምድ ልውውጥ ተካሂዷል፡፡
በልምድ ልውውጡ የተሳተፉት በሚኒስቴር መ/ቤቱ እና ተጠሪ ተቋማቱ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ላይ የሚሰሩ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ ሴት ስራ ፈጣሪዎችን እና ሌሎችም ለልምድ ልውውጡ ውጤታማነት አጋዥ የሆኑ አካላት ተሳትፈዋል፡፡ የልምድ ልውውጡ የተካሄደበት ዓላማ በስራ ፈጠራ /Inovation/ እና በስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ አምራች ተቋማቱ ሴቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር እየሰሩ ያሉትን ስራዎች በማየት ተሞክሮዎችን መለዋወጥ እና በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎችን ሊያጠናክር የሚችል እውቀት ለመገንባት መሆኑን በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የጥራት መሰረተ ልማት ፕሮጀክት የማህበራዊ ደህንነትና የስርዓተ ፆታ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ተሾመ በየነ ገልጸዋል፡፡
የልምድ ልውውጡ የተካሄደው በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን አረካ ከተማ ፣ በደቡብ ክል ጋሞጎፋ ዞን አርባምንጭ ከተማ ፣ በሲዳማ ክልል ይርጋለም ከተማ በሚገኙ አምራች ተቋማት በመገኘት ነው፡፡ ወ/ሮ የኔነሽ አለባቸው በልምድ ልውውጡ ላይ የተሳተፉ ሴት ስራ ፈጣሪ ናቸው፡፡ ወ/ሮ የኔነሽ የመንግስት ሰራተኛ በነበሩበት ወቅት ተቀጥሮ የመስራትን አስከፊነት እና የራስ የሆነን ስራ ፈጥሮ የመስራትን ነፃነትና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አነፃጽሮ በመረዳት ተቀጥረው ይሰሩት የነበረውን የመንግስት ስራ ለቀው በቅቤ ንግድ የተሰማሩ ሲሆን በሂደትም የባልትና ውጤቶችን አቀነባብሮ ኤክስፖርት በማድረግ የግላቸውን ስራ ፈጥረዋል፡፡ የባልትና ውጤት ማቀነባበር ስራውን የጀመሩት በ2,000 ብር ሲሆን በአሁኑ ሰዓት 5 ሚሊዮን ብር ካፒታል ፈጥረዋል፡፡
ቅመማ ቅመም፣በርበሬ፣ ሽሮ፣ ማር እና ቅቤ በማቀነባበር ወደ አሜሪካና ካናዳ ኤክስፖርት የሚያደርጉ ሲሆን ለ13 ሰዎችም የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡ወ/ሮ የኔነሽ ሴቶች የማንንም ድጋፍ ሳይጠብቁ ራሳቸው በሁለት እግራቸው መቆም አለባቸው የሚል አስተሳሰብ አላቸው፡፡ ተፈጥሮ ከወንዶች በተለየ መልኩ ለሴቶች የቸረችው ነገር በመኖሩ በየትኛውም የስራ ዘርፍ ተሰማርተው ሲሰሩ ለሚገጥሟቸው ችግሮች የተለዩ አማራጮችን በመፈተሸ ጥንካሬያቸውን ማሳየት አለባቸው ያሉት ወ/ሮ የኔነሽ ስኬት ያለውጣውረድ ሊመጣ እንደማይችል ከግል ተሞክሯቸው በመነሳት አስረግጠው ተናግረዋለል፡፡አክለውም እንደ ሀገር መንግስት ሴቶች ላይ ሰፊ ስራ መስራት አለበት ያሉ ሲሆን ሴቶች በተፈጥሯቸው ለሙስና የተጋለጡ ባለመሆናቸው በስራ ውጣውረድ ውስጥ የሚገጥሟቸውን ችግሮች የሚያቃልሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጅዎችን መቅረጽ አለበትም ብለዋል፡፡ወ/ሮ ትግስት ከበደ በልምድ ልውውጡ ላይ የተገኙ ሌላኛዋ ስራ ፈጣሪ ናቸው፡፡
ወ/ሮ ትግስት በግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ሲሰሩ ያካበቱትን ክህሎትና እውቀት ተጠቅመው በ1 ሰንጀር እና በ5 ሺብር በቆዳ ዘርፍ የግላቸን ስራ የፈጠሩ ሰሆን ለ9 ሰዎችም የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡ ወ/ሮ ትግስት የሴቶች ቦርሳ፣ ሻንጣ፣ ዋሌት፣ ቀበቶና መሰል የቆዳ ውጤቶችን እያመረቱ ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረቡ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት 1.7 ሚሊዮን ብር ካፒታል አላቸው፡፡ በቀጣይ በሽመና ዘርፍም ለመሰማራት ውጥን አለኝ ያሉት ወ/ሮ ትግስት ከልምድ ልውውጡ አቅሜን እንዳይና የበለጠ መጠንከር እንዳለብኝ ተገንዝቤያለሁ ብለዋል፡፡
በልምድ ልውውጥ መረሀ-ግብሩ በሴቶች ስራ አመራር ማሰልጠና ማኑዋል (weman leadership training manuale) እና በስርዓተ ፆታ አካታችነት ማሰልጠኛ ማኑዋሎች/ Gender mainstreaming training manuale / ዝግጅት ላይ ለተሳተፉ 16 አመራሮችና ባለሙያዎች የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡