ህገ ወጥ የቁም እንሰሳት ግብይትን በመግታት የሃገርን ብሄራዊ ጥቅም ማስከበር ይገባል!
==========================================
ከኢትዮጲያ ስታስቲክስ ኤጀንሲ በተገኘው መረጃ መሠረት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2020/21 ሃገራችን 70.2 ሚሊዮን የዳልጋ ከብቶች፣52.5 ሚሊየን ፍየሎች፣42.9 ሚሊየን በጎችና 8.1 ሚሊየን ግመሎች እንዳሏት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህም ሃገራችን በእንስሳት ሀብቷ ከአፍሪካ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ እንድትሆን አድርጓታል፡፡
ነገር ግን ሃገራችን የዚህ ሁሉ ዕምቅ ሀብት ባለቤት ብትሆንም ይህንን ዕምቅ ሃብቷን በአግባቡ እየተጠቀመችበት እንዳልሆነ ያሉት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህም በምክንያትነት በርካታ ጉዳዮች ይነሳሉ፡፡ ከነዚህ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ህገ ወጥ የእንሳሳት ንግድ እንቅስቃሴ ሲሆን መንግስት የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ለዚህ ችግር እልባት ለመስጠት መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ቢሆንም የተፈለገው ለውጥ መጥቷል ብሎ በድፍረት መናገር አይቻልም፡፡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት፤ ከጉምሩክ ኮሚሽን እና ከሚ/ር መስሪያ ቤቱ የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን በማዋቀር የዳሰሳ ጥናት አካሂዷል፡፡
አቶ በላይሁን ማሞ በሚኒስቴር መ/ቤቱ ከጥናት ቡድኑ አንዱ ሲሆኑ የዚህ ጥናት ተቀዳሚ ዓላማ ህገ ወጥ የቁም እንሰሳት ንግድ ሃገሪቱን ከወጪ ንግድ የምታገኘውን ገቢ በመቀነስ በሃገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ላየ እያደረሰ ያለውን ጫና ማሳየት እና ለችግሩም ዘመኑን የሚመጥን እልባት ለመስጠት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዚህ ህገ ወጥ የእንሳት ንግድ መነሻ ቦታ ኦሮሚያ፤ አማራና ደቡብ ክልሎች ሲሆኑ እንሰሳቱ በቡሬ ማንዳና በአፋምቦ በሮች እና የጉምሩክ ኬላ በሌለባቸው ቦታዎች በህገ ወጥ መልኩ በተሸከርከሪ ተጭነው እና በእግር እየተነዱ ወደ ጎረቤት ሀገራት ይወጣሉ፡፡ ለዚህ ህገ-ወጥ ድርጊት መባባስ በዋናነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል ውስን ግለሰቦች ከሃገራቸው ብሄራዊ ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን እላፊ ተጠቃሚነት ብቻ ለማካበት የሚያደርጉት ያልተገባ ድርጊት ዋንኛው ነው፡፡
በጉምሩክ የፍተሻ ኬላዎች የቁጥጥርና የክትትል ሂደት ማነስ ሌላው የችግሩ መንስኤ ሲሆን ከነዚህ ኬላዎች ውስጥም አዋሽ ፣ሚሌ እና ሰመራ (ሰርዶ ሜዳ፣አሳይታ) ከጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች መካከል ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ በነዚህ የፍተሻ ጣቢያዎች ለቁጥጥሩ ማነስ መንስኤ ናቸው ተብለው የተጠቀሱ ጉዳዮች ደግሞ ወደ አገር የሚገባ እቃ እንጂ ወጪ እቃዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል አካሄድ አለመኖሩ፤ የግንዛቤ እጥረት መኖሩ፣ ለእንሰሳቱ የማቆያ ቦታ ፤የመኖ እና የውሃና መኖ እጥረት መኖሩ እንሰሳቱ ቢያዙ እንኳን የሚያመጣውን ከፍተኛ ኪሳራ በመፍራት ህገ ወጥ እንቅስቃሴውን ለማስቆም የተነሳሽነት ማነስ የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው፡፡
የዚህ ህገ ወጥ ተግባር መስፋፋት ሃገሪቱ የምታገኘውን የውጪ ምንዛሬ ከማሳጣት በተጓዳኝ በሃገራችን ተገንብተው በስራ ላይ የሚገኙ የኤክስፖርት ቄራዎች የእርድ እንሳሳት የአቅርቦት ችግር እንዲገጥማቸው ምክንያት መሆኑ አጠያያቂ አይደለም ፡፡ አሁን በስራ ላይ ያሉት የቄራ ፋብሪካዎች የእርድ እንስሳት ፍላጎት በአመት 12 ሚሊዮን በግና ፍየል እንዲሁም 1.3 ሚሊዩን የዳልጋ ከብት ፍላጎት አላቸው፡፡
በአንጻሩ እየቀረበላቸው ያለው 1.79 ሚሊዮን በግና ፊየል እና 2,260 የዳልጋ ከብት ብቻ ነው፡፡ ይህም የቄራዎች ፍላጎት እና የእንስሳት አቅርቦት ተመጣጣኝ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡የጥናት ቡድኑ ለተነሱት ችግሮች የመፍትሄ ሃሳቦችን ያስቀመጠ ሲሆን ከተቀመጡት የመፍትሄ ሃሳቦች ውስጥ በቁም እንስሳት አዋጅ ደንብና መመሪያዎች ለአርብቶ አደር ማህበረሰብ ግንዛቤ የመፍጠር ስራን መስራት፣ የፀረ-ኮንትሮባንድ ግብረ ሀይል የቁጥጥር ስርዓትን አጠናክሮ መቀጠል ፣በህገ ህገ-ወጥ መልኩ ሲጓጓዙ የተገኙ እንሰሳትን የማቆያ ቦታዎችን እና የምግብ አቅርቦትን ማመቻቸት፣ በክልል የጸጥታ ፣በጉምሩክ ኮሚሽን እና በፌደራል ፖሊስ አካላት መካከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማሳደግ፣ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከላትን በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ማድረግ እና በጥናት ላይ ተመስርቶ ሌሎች ተጨማሪ ኬላዎችን ማቋቋም የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡በአጠቃላይ ለኮንትሮባንድና ለህገ ወጥ የቁም እንሰሳት ንግድ በርካታ ምክንያቶች ተነስተዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ የመፍትሄ ሃሳቦች በጥናቱ ላይ የተመላከቱ ሲሆን ለነዚህ የመፍትሄ ሃሳቦች የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና የላቀ ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሃገርን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር የሚደረገውን ጥረት መደገፍ ይኖርበታል፡፡