የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ቁጥጥር ስርዓቱን ለማሻሻል ከአስፈፃሚ አካላት ጋር ምክክር ሊያደርግ ነው፣

የንግድ ስርዓት በጥራት መሰረተ-ልማት አገልግሎት ሰጭ ተቋማትና

በተቆጣጣሪ አካላት መካከል የተቀናጀ አሰራር ሲኖረው የምርትና አገልግሎት ጥራት ደረጃ እንዲጠበቅ፣ ምርታማነትን በመጨመር የኢኮኖሚ እድገት እንዲመጣ እንደሚያስችል ያደጉ ሀገራት ተሞክሮ ያሳያል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም በፌዴራል መንግስት የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 መሰረት የወጪና ገቢ ንግድ እቃዎችን ጥራት የመቆጣጠር፣ ተፈላጊውን የደረጃ መስፈርት የማያሟሉ የንግድ እቃዎች ከሀገር እንዳይወጡ ወደ ሀገርም እንዳይገቡ የመከታተል ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

አስገዳጅ የኢትዮጰያ ደረጃ ያላቸው የንግድ እቃዎችና አገልግሎቶች የደረጃውን መስፈርት ማሟላታቸውን መቆጣጠር፣ በሌሎች አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች የሚሰራባቸው አስገዳጅ ደረጃዎች በተቀናጀ መልኩ እንዲተገበሩ ማድረግ እንዲሁም የሀገሪቱን ህጋዊ ስነ-ልክ ስርዓት ለመተግበር አስፈፃሚ አካላትን ማስተባበርም ለሚስቴር መ/ቤቱ የተሰጡ ተግባርና ኃላፊነቶች ናቸው፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እነዚህን ኃላፊነቶቹን በተሻለ መልኩ ለመወጣት ይረዳው ዘንድም አስፈፃሚ አካላቱ ተቀናጅተው የሚሰሩበትን ሥርዓት በመቀየስ አሁን ያለውን የንግድ ቁጥጥር ሥርዓት ለማሳለጥ ከአስፈፃሚ አካላት ጋር የሚካሄድ የምክክር መድረክ ለግንቦት 10 ቀን/2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል አዘጋጅቷል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የሚገኙት የአስፈፃሚ ተቋማት ኃላፊዎች እና የህግ አገልግሎት ኃላፊዎቻቸው ሲሆኑ በምክክሩ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ የመግባቢያ ሰነድ ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Share this Post