የዋጋ ንረትን መቀነስ ዓላማ ያደረገው የቅዳሜና እሁድ ገበያ

አዲስ አበባ (ንቀትሚ) 22/09/2014 በሀገራችን የሸቀጦች ዋጋ ንረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ይገኛል፡፡ ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው የሚያዝያ ወር 2014 ዓ/ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 36.6% ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ምግብ ነክ ያልሆነው የዋጋ ንረት  28.1% የደረሰ ሲሆን በዚህ ወር የምግብ ነክ ዋጋ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ42.9% ጭማሪ አሳይቷል፡፡

  የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ፈጥሮት የነበረው ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ የምርት መስተጓጎል፣የሕውሓት ሽብር ቡድን በከፈተው ጦርነት ሀገሪቱ የገባችበት የህልውና ዘመቻ እና የኢኮኖሚውን መዋቅር ለማዳከም ኢትዮጵያን የካዱ አካላት የፈጠሩት ምጣኔሀብታዊ አሻጥር ለዋጋ ግሽበቱ ምክንያት ከሆኑት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ዓለም አቀፋዊ የምጣኔ ሀብት ምክንያቶች እና የሩሲያና የዩክረሬን ጦርነት በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ያደረጉት ሰሆን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተብ ክፍሎች ደግሞ በዋጋ ግሽበቱ ክፉኛ ተጎጂ ሆነዋል።

 መንግስት ይህንን ችግር ለመፍታት በርካታ የአጭር ጊዜ እና የረጅም ጊዜ መፍትሄ አምጭ እቅዶችን አዘጋጅቶ መተግበር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ከውጪ ሲገቡም ሆነ ሀገር ውስጥ ሲገበዩ ከቀረጥና ታክስ ነፃ ኢንዲሆኑ በመወሰን መንግስት የሚያገኘውን ገቢ ትቶ  የዋጋ ጫናውን ከሸማቹ ህብረተሰብ ላይ ለማቃለል ጥረት ተደርጓል፡፡

ኃላፊነት የማይሰማቸው ነጋዴዎች ምርት ያለአግባብ በማከማችትና እጥረት ያለ በማስመሰል የሚፈጥሩት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለሽ የዋጋ ንረት እንዲሁም በደላላዎችና ህገ-ወጥ የንግድ ተዋንያን አማካኝነት ያለው የተንዛዛ የግብይት ሂደት በምግብ ሸቀጦች ላይ እየተከሰተ ያለውን የዋጋ ንረት ለማርገብና ዝቅተኛ ገቢ በላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለማቃለል የቅዳሜና እሁድ ገበያ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

የቅዳሜና እሁድ ገበያ የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶች በአጭር የግብይት ሂደት ከአምራቹ በቀጥታ ለሸማቹ በተመጣጠነ ዋጋ የሚቀርብበት ፕላት ፎርም ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የተጸነሰው ይህ ፕላት ፎርም አስፈላጊነቱና ችግርፈችነቱ ስለታመነበት የአተገባበር ማኑዋል ተዘጋጅቶለት ድሬዳዋ ከተማን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ ሆኗል፡፡

 ግብይቱ በየሳምንቱ በዕለተ ቅዳሜ እና እሁድ የሚከናወን ቢሆንም በሲዳማ ክልል በሳምንት ባሉት ሰባቱም  ቀናት ነው ተግባራዊ የተደረገው፡፡ በክልሉ ካሉ 53ሺ የሸማቾች ህብረት ሰራ ማህበራት ውስጥ አቅም ያላቸውን 29 ማህበራት በመለየትና ፕሮግራም/ተራ/ በመስጠት ሳምንቱን ሙሉ ምርቶችን እንዲያቀርቡ በማድረግ ግብይቱ መጀመሩን ከክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 ግብይቱ ከመደበኛው ገበያ ዋጋ ቅናሽ በበለጠ ተስፋፍቶ መቀጠል አለበት ሲሉ በሐዋሳ ከተማ የቅዳሜ ገበያ ሲሸምቱ አግኝተን ያነጋገርናቸው ሸማቾች ነግረውናል፡፡ ሁሉንም የከተማዋ ነዋሪ ተጠቃሚ ለማድረግ አሁን ካለው በተጨማሪነት በየአካባቢው የግብይት ማዕከላት በመክፈት መስፋፋትና መጠናከር አለበት ሲሉ ሸማቾቹ አስተያታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የሐዋሳ ከተማ ኃ/የተ/ሸ/ህ/ማህበር ዩኒዮን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ሳሞኤ በበኩላቸው የከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የመጣው የዋጋ ንረት በማህበረሰቡ ላይ የሚፈጥረውን ጫና ለመቀነስ መንግስት የቀየሰውን የመፍትሄ አማራጭ በመጠቀም የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶችን ከአንድ ብር በማይበልጥ የትርፍ ህዳግ ለተጠቃሚው እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሚያቀርቡትን የምርትና አገልግሎት አይነት ለማስፋትና የግብርና ምርቶችን ከገበሬው ማሳ ላይ ገዝቶ ለማቅረብ ከፍተኛ የሆን የገንዘብ እጥረት እንዳለባቸው አቶ ሳሞኤል ገልጸዋል፡፡ ብክትማው ውስጥ በርካታ ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ቢኖሩም ባለባቸው የአቅም ውስንነት ምክንያት ሁሉም በቅዳሜና እሁድ ገበያ ላይ አልተሳተፉም ያሉት አቶ ሳሞኤል ሁሉንም ቦታዎች ለማዳረስ የሀሚያስችል አቅም እንደሌላቸው ገልጸው የድንኳንና የገንዘብ ድጋፍ ካገኙ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በማቅረብ ህብረተሰቡን ለመገልገል ማህበራቱ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

መንግስት የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራትን የፋይናንስ ችግር ለማቃለል እየሰራ ቢሆንም ከዚህ ቀደም 6ሚሊዮን ብር ብድር ጠይቀው ዘጠኝ መቶ ሽህ ብር እንደተፈቀደላቸው ጠቅሰው  ይህ ደግሞ ከፍላጎቱ አንፃር ኢምንት ነውም ብለዋል፡፡ ዩኒዮኖችና ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ለህዝብ አገልጋይ እንደመሆናቸው መጠን  አበዳሪ የፋይናንስ ተቋማት ብድር የሚሰጡበትን ቢሮክራሲ በማቃለልና ብድር በመስጠት ተቀራርበው በመስራት ሊደግፉ እንደሚገባም የቦርድ ሰብሳቢው ጠይቀዋል፡፡

የቅዳሜና እሁድ ገበያ የተጀመረው የኑሮ ውድነቱ በትር በሚበረታባት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ጅምሩም በየሳምንቱ እሁድ ቀን ብቻ የነበረ ሲሆን የዋጋ ንረትን በማርገብ ረገድ ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑ በመረጋገጡ ወደሌሎች ክልሎችም ተስፋፍቶ እሁድ ብቻ የነበረው ቅዳሜንም ጨምሮ ተደራሽነቱን ለማስፋት የተጠናከረ ስራ ተሰርቷል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት በተጨማሪ የቅዳሜና እሁድ ገበያ የተቋቋመበትን ዓላማ የተቀበሉ ግለሰብ ነጋዴዎችም በምርት አቅራቢነት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ አቶ ኤፍሬም  በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 የአትክልትና ፍራፍሬ ነጋዴ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በእሁድ ገበያ ላይ ምርት እያቀረቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ በወረዳው ከተፈቀደላቸው ነጋዴዎች ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡

ዋጋ ለማረጋጋት በእሁድ ገበያ ላይ በአቅራቢነት ተመርጠው እያቀረቡ በመሆኑ ከገንዘብ ትርፍ በላይ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ስለሆነ ደስተኛ መሆናቸውን በመገናኛ አካባቢ ባለው የእሁድ ገበያ ተገኝተን ባነጋገርናቸው ወቅት ገልጸውልናል፡፡ በመደበኛው ገበያ ከሚሸጡበት ዋጋ በቀነሰ መልኩ በአንድ ብርና በሁለት ብርት ትርፍ በእሁድ ገበያ እየሸጡ መሆኑን የገለጹት አቶ ኤፍሬም አቅርቦቱን ለማሳደግ እና ለሌሎች ወጣቶችም የስራ እድል ለመፍጠር ማሳ ላይ ሰፊ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

 በዚሁ የግብይት ቦታ ሲሸምቱ ያገኘናቸው መቶ አለቃ ኃይሉ ኪዳኔ እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ሰብለወርቅ ተስፋዬ በበኩላቸው መንግስት የዘረጋው የእሁድ ገበያ ከመደበኛው ገበያ ዋጋ ቅናሽ በመሆኑ እንደጠቀማቸው ገልጸው ሊበረታታና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋልም ብለዋል፡፡ የእሁድና ቅዳሜ ገበያ ባይመጣ ኖሮ በየቀኑ እየጨማረ ያለውን የዋጋ ንረት ተቋቁመን መኖር አንችልም ነበር ያሉት ጥንዶቹ ርቀት አቋርጠን ስለምንመጣ የታክሲ ወጪው ስለሚጎዳ በየአካባቢው ቢከፈት ህብረተሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በተለይ በለሚ ኮራ ይከፈታል ተብሎ ተነግሮ ነበር ሆኖም ተግባራዊ ስላልሆነ ርቀት ቦታ ሄደው ለመገብየት መገደዳቸውን ገልጸው በየአካባቢው ተስፋፍቶ ሸማቹ ህብረተሰብ ብዙ የትራንስፖርት ወጪ ሳያወጣ ማግኘት የሚችልባቸው ስራዎች መሰራት አለባቸው የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

ሲጠቃለል የቅዳሜና እሁድ ገበያ በተለይም ያለኢኮኖሚያዊ ምክንያት እየጨመረ ያላውን የዋጋ ንረት በማርገብ ረገድ ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡  አምራቾች ሰፊ የገበያ እድል፣ ሸማቾች ደግሞ ያለደላላ ጣልቃ ገብነት በአጠረ የግብይት ሂደት በተመጣጠነ ዋጋ እንዲሸምቱ አስችሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የተደራሽነት ውስንነት አለበት፡፡

 የግብይት ቦታዎቹ ውስን ከመሆናቸው የተነሳ ህብረተሰቡ ርቀት ያለው መንገድ የታክሲ ትራንስፖርት ከፍሎ በመሄድ የሚያገኘው ገበያ እምብዛም ተጠቃሚ አያደርገውም፡፡ ይህንንም በአዲስ አበባ እና በሐዋሳ ከተሞች በሚገኙ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ላይ ተገኝተን ከሸማቹ ህብረተሰብ ክፍል ባገኘነው አስተያየት አረጋግጠናል፡፡

በሌላ በኩል ይህ የግብይት ፕላት ፎርም በጅምሩ ወቅት የተሰጠው ትኩረትና ርብርብ አብሮት የዘለቀ አይመስልም፡፡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የግብይት ሂደቱ በማኑዋል ተደግፎ ስርዓት እየተበጀለት በመላው ሀገሪቱ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየሰራ ይገኛል፡፡ የከተማ አስተዳር፣ የክልልና በየተዋረዱ ያሉ የዘርፉ አስፈፃሚ አካላትም የቅዳሜና እሁድ ገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት ብዙ ስራዎችን መስራት ይጠይቃል፡፡ የዋጋ ንረቱ አሁንም ማብቂያ እስካላገኘ ድረስ ይህንን ጉዳይ መቸም ቢሆን ትኩረት ልንነሳው አንችልም፡፡

Share this Post