የገና እና የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ የአቅርቦት እና የዋጋ ንረት እንዳያጋጥም ዝግጅት ተደርጓል፡፡

የገና እና የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ የአቅርቦት እና የዋጋ ንረት እንዳያጋጥም ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ==================== አዲስ አበባ 25/04/2016ዓ.ም (ንቀትሚ) የገና እና የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ የፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በመሆን በቂ አቅርቦት እንዲኖር ዝግጅት የተደረገ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ስርዓትና ላይሰንሲንግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍሰሃ ይታገሱ በመንግስት የሚቀርብ የምግብ ዘይት ከዚህ በፊት ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ያልተሰራጨ 9.8 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በመንግስት የልማት ድርጅቶች እንዲሁም 8.6 ሚሊዮን ሊትር ዘይትና 3.2 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር በፍራንኮ ቫሎታ ለገበያ እንዲቀርብ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ እንደ ሀገር በተቋቋሙ ከስምንት መቶ በላይ የቅዳሜና እሁድና ገበያዎች አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች የፋብሪካ ውጤቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ሳምንቱን ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጋውን ጠቁመዋል፡፡ ዋጋን ለማረጋጋት በተሰራው ቅንጅታዊ አሰራር መሰረት ከ8 ሚሊዮን በላይ እንቁላል ለገበያ እየቀረበ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1.7 ሚሊዮን አዲስ አበባ ከተማ፣ በአማራ ክልል 8 መቶ ሺ፣ በኦሮሚያ 5 ሚሊዮን፣ ደቡብ ኢትዮጵያ 1.3 ሚሊዮን እና ሌሎች ክልሎች ከ2 ሚሊዮን በላይ እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡ ለበዓል ገበያው ከ800 ሺ በላይ ፍየልና በግ ለገበያ የቀረበ ሲሆን፣ ከ1 ሚሊዮን በላይ ዶሮ እንዲሁም ከ500 ሺ በላይ ሰንጋዎች ለገበያ ቀርበዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከ1084 በላይ፣ በኦሮሚያ ከ313 ሺ በላይ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ከ59 ሺ በላይ የደለቡ ሰንጋዎች ለገበያ ቀርበዋል፡፡ እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ በ2ሺ 710 የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ስጋ ቤቶች ለበዓል በኪሎ ከ450 ብር ጀምሮ ስጋ ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

Share this Post