የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ፍትሀዊ የሆነ እኩል የውድድር ሜዳ ይፈጥራል

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ፍትሀዊ የሆነ እኩል የውድድር ሜዳ ይፈጥራል ========================== አዲስ አበባ 27/06/2016ዓ.ም (የንቀትሚ) ኢትዮጵያ እየተሳተፈችበት ያለው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና/AfCFTA/ ድርድር ተጠናቆ ተግባራዊ ሲደረግ ለሀገራችን የንግድ ማህበረሰብ እና ኢንዱስትሪዎች ፍትሀዊ የሆነ እኩል የውድድር ሜዳ ይፈጥራል፡፡ በፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መነሻነት የተመሰረተው አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ካሉት መርሆዎች ውስጥ “የአንድን ሀገር ምርት ከሌላው ሀገር ምርት ጋር እኩል ማስተናገድ” ፣ “የሀገር ውስጥ ምርትን ከአባል ሀገራቱ ከሚገቡ ምርቶች ጋር እኩል ማስተናገድ” የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በዚህ መሰረትም ለሀገራችን ኢንዱስትሪዎች እና የንግድ ማህበረሰብ አካላት ምርቶቻቸውን በሀገር ውስጥም በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም አኩል የመወዳደር እድል እንደሚሰጥ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊት ንግድ ትስስር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታገስ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡ ስምምነቱ የአፍሪካ ሀገራትን የእሴት ሰንሰለት በማጠናከር የኢንዱስትሪ ግብአት ለማግኘትም ያስችላል ያሉት አቶ ታገስ የሀገራችን ኢንዱስትሪዎች እና የንግድ ማህበረሰብ አካላት በዚህ የንግድ ስርዓት ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት እና በሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ተጠቃሚ ለመሆን ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባቸውም አመልክተዋል፡፡ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የምርትና አገልግሎት ጥራትን ማሻሻል እንዲሁም ምርትን ማስተዋወቅ እና የግብዓት አቅርቦት ለማግኘት ከሀገራት ጋር ትስስር መፍጠር እንዳለባቸው ነው መሪ ስራ አስፈፃሚው ያስረዱት፡፡

Share this Post