የሰንበት ገበያ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ሚናው ጉልህ መሆኑ ተጠቆመ ።

የሰንበት ገበያ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ሚናው ጉልህ መሆኑ ተጠቆመ ። ================= አዲስ አበባ 07/08/2016ዓ.ም (ንቀትሚ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ የሰንበት ገበያ ሂደትን ተዘዋውረው የመስክ ምልከታ አድርገዋል። ሚኒስትሩ በመስክ ምልከታው ወቅት እንደገለፁት ከሰንበት ገበያ ሸማቹ ማህበረሰብ በቅናሽ ዋጋ የምግብ ፍጆታዎችን መግዛት በመቻሉ የሰንበት ገበያ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ሚናው ጉልህ ነው። በሆሳዕና ከተማ የሰንበት ገበያ በቅዳሜና እሁድ ብቻ የተገደበ ሳይሆን በየዕለቱ የግብይት ስረዓቱ የሚፀምበት መሆኑ ከሌሎች ከተሞች ለየት ያደርገዋል ያሉት ሚኒስትሩ በከተማው ውስጥ በርካታ የመሸጫ ሼዶች መኖራቸውንም አድንቀዋል። መንግስት የሌማት ቱሩፋት ፕሮግራምን በማውጣት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለሸማቹ ማህበረሰብ በቅናሽ የምግብ ፍጆታ እንዲቀርብ መደረጉን የተናገሩት ሚኒስትር ገ/መስቀል የገበያ መረጃ ማጠናከር ይገባል ሲሉም አሳስበዋል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው በበኩላቸው የሰንበት ገበያ ከሰንበት እስከ ሰንበት ሻጩና ሸማቹ ማህበረሰብ የሚገበያዩበት መሆኑን ተናግረዋል። በክልሉ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ከ100 በላይ የሰንበት ገበያ ማቋቋም መቻሉንም ኃላፊው ገልፀዋል። የኑሮ ውድነት ንረትን የሚያመጡ የህግ ወጥ የእህል መጋዘን ክምችን የመቆጣጠር ስራ በልዩ ትኩረት አየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዳንኤ በ217 ህገ ወጥ የእህል መጋዘንን ማሸግ መቻሉንም ጠቅሰዋል። የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሰንበት ገበያን ከማቋቋም ጎን ለጎን የህገ ወጥ የምርት ክምችት ላይ ህጋዊ እርምርጃ እየተወሰደ እንደሚገኝም ኃላፊው ጠቁመዋል ሲል የዘገበው የክልሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ። ሚኒስትሩ በሆሳዕና ከተማ ቆይታቸው የጅምላና ችርቻሮ ነጋዴዎች ገበያ ላይ ጤፍ ፣በቆሎ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ የሰንበት ገበያ፣ ሊቻ የገበሬዎች ማህበር ፣አለቻ ከብት እርባታ እና ሌሎች ማዕከላትንም ተዘዋውረው የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

Share this Post