በድሬዳዋ በአምራች ኢንዱስትሪዎች የተመረቱ የፍጆታ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበባቸው ነው

በድሬዳዋ በአምራች ኢንዱስትሪዎች የተመረቱ የፍጆታ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበባቸው ነው ================= አዲስ አበባ13/08/2016(ንቀትሚ) በድሬዳዋ በአምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ የተመረቱ የፍጆታ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ፍሰሃ ይታገሱ አመለከቱ። በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ፍሰሃ ይታገሱ የተመራ ቡድን በድሬዳዋ አስተዳደር በኢንዱስትሪና በንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ የታዩ ለውጦችን ተመልክቷል። ቡድኑ በአስተዳደር ደረጃ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል በሸማቾች ማህበራት እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራትንና ባሉ ክፍተቶች ላይ ከማህበራቱ፣ እንዲሁም በአስመጪና በአከፋፋይ የንግድ ስራ ከተሰማሩ አካላት ጋር ተወያይቷል። የሸቀጦችን ዋጋ በማረጋጋት ተግባራት ላይ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ የሚገኘውን የቅዳሜና የእሁድ ገበያንም ተመልክቷል። በተጨማሪም በድሬዳዋ አስተዳደር በነፃ ንግድ ቀጣና ውስጥ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ ለማምረት እየተካሄዱ የሚገኙ የአምራች ኢንዱስትሪዎች እንቅስቃሴዎችንም ጎብኝቷል። አስተዳደሩ የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን ወደ ኢንቨስትመንት ስራ ለማሸጋገር እያከናወናቸው የሚገኙ ስራዎችንም ተመልክቷል። በሚኒስትር ዴኤታው የተመራው ቡድን ድጋፋዊ የስራ ጉብኝቱን በአስተዳደሩ ኢንዱስትሪ መንደር በአምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ እየተካሄዱ የሚገኙ የልማት እንቅስቃሴዎችንም በመመልከት ማምሻውን አጠናቋል። ሚኒስትር ዴኤታው ከጉብኝቱ በኋላ እንደተናገሩት በአስተዳደሩ የምርት አቅርቦትን በማሳደግና ለሸማቾች በማቅረብ የኑሮ ወድነትን ለማቃለል እየተከናወኑ የሚገኙ የተቀናጁና የተናበቡ ስራዎች አበረታች ናቸው። ጅምሩን ለማጠናከር በሸማቾች ማህበራትና ዩኒየኖች ላይ የሚስተዋለውን የገንዘብ ክፍተት በመፍታትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይገባል ብለዋል። በአምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረትና በቂና ተመጣጣኝ የፍጆታ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ረገድ እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን አስተውለናል ብለዋል። በድሬዳዋ ወደ አገልግሎት የተሸጋገሩ የደረቅ ወደብና የነፃ ንግድ ቀጣና እንቅስቃሴዎች ድሬዳዋ የምስራቅ የሀገራችን ከፍል የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል የማድረጉ ስራ በስኬት ጎዳና ላይ መሆናቸውን ያመለክታሉ ሲሉም አክለዋል። በተለይ አስተዳደሩ ባለው ውስን በጀት ለአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ሼዶች በመገንባትና የገበያ ትስስር በመፍጠር ወደ ኢንቨስትመንት ስራ እንዲሸጋገሩ እየሰራቸው የሚገኙት ተግባራት በተሞክሮ ተቀምረው የሚስፋፉ እንደሚሆኑ ገልጸዋል። የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የፌዴራል መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። በስራ ጉብኝቱ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህና የድሬዳዋ የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አመራሮች ተሳትፈዋል።

Share this Post