የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ከቱርክ አምባሳደር ጋር ተወያዩ
=======================
አዲስ አበባ 08/09/2016ዓ.ም (ንቀትሚ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ከቱርክ አምባሳደር ጋር የኢትዮጵያን እና የቱርክን የንግድ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
የግብርና ምርቶችን ወደ ቱርክ በመላክ እና የግሉን ሴክተር ግንኙነት( B2B) በማጠናከር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ሚዛን ክፍተት ማጠበብ እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሩ በውይይታቸው አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሴክተሯን ለውጪ ባለሀብቶች ክፍት እያደረገች በመሆኑ የቱርክ ባለሀብቶች መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ቱርክ በንግድና ኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ እና በአቅም ግንባታ ልምዷን እንድታካፍል የጠየቁት አቶ ገብረመስቀል የቱርክ ባለሀብቶች በሀገራችን በንግድና ኢንቨስትመንት ለሚያደርጉት ተሳትፎ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግም አመላክተዋል፡፡
የቱርክ አምባሳደር ሚስተር በርክ ባራን በበኩላቸው ኢትዮጵያና ቱርክ ዘመናትን የተሻገረ የንግድና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አላቸው ያሉ ሲሆን በቱርክ ገበያ ቡና፣ የቆዳ ውጤቶች እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ ምርቶች ፍላጎት እንዳለ ገልጸዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራትን የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት በእጅጉ ለማጠናከር ሁሉንም የንግድና ኢኮኖሚ ጉዳዮች በአንድ መድረክ አምጥቶ ለመምከር የሚያስችል የጋራ የኢኮኖሚ ኮሚሽን ለማካሄድ ከስምምነት ደርሰዋል።