የተቀናጀ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ለመፍጠር የሚያስችል የጋራ ስምምነት ተፈረመ።
=====================
አዲስ አበባ 07/09/2016ዓ.ም (ንቀትሚ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተቀናጀ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ለመፍጠር የሚያስችለውን የጋራ ስምምነት ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት ጋር ተፈራረመ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሀገሪቷን የንግድ ስራ አመችነት ለማሻሻል ባከናወናቸው በርካታ የሪፎም ስራዎች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው በ2013 ዓ.ም የተጀመረው ኦን ላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ በእጅጉ አድጎ በተያዘው በጀት ዓመት 9 ወራት ከ 1.9 ሚሊዮን በላይ አገልግሎቶች ለነጋዴው ህብረተሰብ በኦንላይን መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
ዛሬ የተፈረመው የጋራ ስምምነት የንግድ መለያ ቁጥር፣ የግብር ደረሰኝ፣ የብቃት ማረጋገጫ የምስክረ ወረቀት፣ ብሔራዊ መታወቂያ እና ሌሎችም ሰነዶችን አውቶሜት በማድረግ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን እውን ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ስራ አስፈፃሚ አቶ ጸጋው በለጠ ከኦንላይን የንግድ መዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ጀምሮ ዲጂታላይዜሽን ላይ ተቋሙ እየሰራ ያለው ስራ ኢትዮጵያ ለንግድ ስራ ያላትን አመችነት በከፍተኛ ደረጃ ያሻሽለዋል ያሉ ሲሆን በተደረገው ስምምነት መሰረት ስራዎች በቅንጅት ተሰርተው አውቶሜት ሲሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ፈቃድ በአማካኝ በአንድ ቀን ማውጣት ይቻላል ብለዋል፡፡
ስምምነቱ ከፈረሙ ተቋማት ውስጥ የገቢዎች ሚኒስቴር፣የሰነዶች ማረጋገጫ፣ ብሄራዊ መታወቂያ፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ይገኙበታል፡