የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ “የኢትዮጵያን ይግዙ” ልዩ የንግድ ሳምንት ኢግዚቪሽንና ባዛር ጎበኙ፡፡
አዲስ አበባ ነሐሴ 22/2016ዓ.ም (ንቀትሚ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር “የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀውን ልዩ የንግድ ሳምንት ኢግዚቪሽንና ባዛር ጎብኝተዋል፡፡
ኢግዚቪሽንና ባዛሩ በተለያዩ የመንግስት ተቋማትና ግለሰቦች እየተጎበኘ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ሌሎች የተለያዩ የከተማዋ ቢሮ ኃላፊዎች ጉብኝት አድርገዋል፡፡
በከንቲባዋ የተመራው የጎብኝ ቡድን የወጪ ንግድ ማሳያ ማዕከሉን ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን በወጪ ምርቶች ማሳያ ማዕከሉና አጠቃላይ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴና መዳረሻ ሀገራት በተለያዩ ባለሙያዎች ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡
ከንቲባዋ በጉብኝታቸው መጨረሻ በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያን ይግዙ የንግድ ሳምንት ሀገራችን ያሏትን ምርቶች ከማስተዋወቅ ባሻገር ህዝባችን በሀገር ምርት እየኮራ የሀገር ውስጥ ምርቶችን በመግዛት ከውጪ የሚገባው እንዲቀንስ እና የውጪ ምንዛሪን እንዲቆጥብ የበኩሉን አስተዋጽዖ ማበርከት የሚያስችል በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሰራው ስራ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል፡፡