የእሁድ ገበያዎች አገር አቀፍ የደረጃ መስፈርት ወጣላቸው፡፡

አዲስ አበባ መስከረም 14/2017 ዓ.ም (ንቀትሚ) የእሁድ ገበያዎች አገር አቀፍ የደረጃ መስፈርት የወጣላቸው መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የእሁድ ገበያዎች አምረቾችን፣ አቅራቢዎቸንና ሸማቾችን ያለደላላ ጣልቃ ገብነት በቀጥታ በማገኛኘት የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ አማራጭ ገበያ ሆነው እንዲያገለግሉ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉን በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሀገር ውስጥ ንግድና ሸማቾች ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ መስከረም ባህሩ ገልፀዋል፡፡ መሪ ስራ አስፈፃሚዋ የእሁድ ገበያዎቹ ተቀራራቢና ወጥነት እንዲኖራቸው እንዲሁም ጥራቱን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት ለሸማቹ ለማቅረብ እንዲቻል ለማድረግ የደረጃ መሰፈርቱ መዘጋጀቱን የገለፁ ሲሆን መስፈርቱ በዋናነት ተግባራዊ የሚሆነው በእሁድ ገበያዎቹ የሚቀርቡ በ6 የምርት አይነቶች ላይ እንደሆነና እነሱም አትክልት፣ ፍራፍሬ፣የቅባት እህሎች፣ አገዳና የሰብል ምርቶች፣ የእንሰሳት ተዋፅኦ እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ያካተተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እንደ መሪ ስራ አስፈፃሚዋ ገለፃ ለእሁድ ገበያዎች የሚቀርቡ የተጠቀሱ የምርት አይነቶች በአራት ምድብ ተከፍለው ሳይቀላቀሉ ንፅህናቸውን በጠበቀ መልኩ ለሽያጭ እንዲቀርቡ የሚያደርግና ስለአቅራቢዎች፣ መሸጫ ቦታዎች፣ ለሼዶች፣የመሸጫ ዋጋ ሁኔታን በተመለከተ በደረጃ መስፈርቱ የተካተተ መሆኑንና የደረጃ መስፈርቱ በብሄራዊ የደረጃዎች ካውንስል የፀደቀ መሆኑን አንስተዋል፡፡

Share this Post