ኢትዮጵያ ወደ ቻይና እየላከቻቸው ያሉ የወጪ ምርቶች በየጊዜው እየጨመሩ መምጣታቸው ተገለፀ።
===========
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 29/2017 (ንቀትሚ)፦ኢትዮጵያ ወደ ቻይና እየላከቻቸው ያሉ የወጪ ምርቶች በየጊዜው እየጨመሩ መምጣታቸውን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ገልፁ፡፡
ኢትዮጵያ በቻይና ዓለም አቀፍ የገቢ ንግድ ኤክስፖ እየተሳተፈች መሆኑ የሚታወስ ሲሆን ከኤክስፖው ጎን ለጎን በተካሄደው የቻይና የገቢ ምግብ ግብአቶች ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት አምባሳደር ተፈራ ደርበው ኢትዮጵያ ወደ ቻይና እየላከቻቸው ያሉ የወጪ ምርቶች በየጊዜው እየጨመሩ መምጣታቸውን ገልፀው የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የግብርና ወጪ ንግድ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ የበለጠ እንዲያሳድጉ ጥሪ ቀረበዋል፡፡
አምባሳደር ተፈራ ደርበው እንደገለፁት የቻይና ባለሀብቶች የኢትዮጵያን ምርቶች የመግዛት ፍላጎት ማደጉንና በኢትዮጵያ ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ለመስራት ፍላጎት ላላቸው ባለሀብቶች የተለያዩ ማበረታቻዎች እንደተዘጋጁ ጠቁመዋል፡፡
ቤጂንግ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም የግብርና ወጭ ምርቶችን የማስተዋወቅና ከገዢዎች ጋር ለማገናኘት ዝግጁ መሆኑን አቶ ተፈራ ደርበው መግለፃቸውን በቻይና የኢትዮጵያ ኢምባሲ መረጃ ያመለክታል፡፡