ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ብር ከህገ ወጥ ንግድ ቅጣት ለመንግስት ገቢ ተደረገ

ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ብር ከህገ ወጥ ንግድ ቅጣት ለመንግስት ገቢ ተደረገ ================== አዲስ አበባ 14/05/2016ዓ.ም (ንቀትሚ) ከንግድ ጋር በተያያዘ ከተከናወኑ ህገ ወጥ ተግባራት ቅጣት ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ገንዘብ ለመንግስት ገቢ መደረጉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በንግድና ቀጣናዊ ትስሰር ሚኒስቴር የፀረ ንግድ ውድድርና ህግ ጥሰት መከላከል ዴስክ ኃላፊ አቶ ጌትነት አሸናፊ እንደገለፁት ባለፉት ስድስት ወራት ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል በተከናወኑ ስራዎች የንግድ ህጉን ተላልፈው በተገኙ አካላት ላይ በተወሰደ ህጋዊ የእርምት እርምጃ 1ሚሊዮን 389 ሺ 216 ብር ከ66 ሳንቲም የገንዘብ ቅጣት ወደ መንግስት ካዝና ገቢ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ 22 አቤቱታዎች መቅረባቸውን የጠቆሙት አቶ ጌትነት 15 አቤቱታዎች ውሳኔ እንደተሰጣቸው አብራርተዋል፡፡አሳሳች ምልክት መጠቀም፣ያልተገባ ውህደት መፈፀም፣በስምምነት ዋጋን መወሰን፣ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ እንደሚገኙበት ገልፀዋል፡፡ ሸማቾች ባቀረቡት አቤቱታ 361ሺ ብር የሆነ የንግድ ዕቃ እንደሸማቾች ፍላጎት ገንዘባቸውን የማስመለስ እንዲሁም ተለዋጪ እቃ እንድሰጣቸው መደረጉን አክለዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሸማቹን ህብረተሰብ ጤንነትና ደህነነት ለመጠበቅ በትኩረት እየሰራ እንደሆነ በመጠቆም ሸማቹ ከንግድ እቃ ጋር በተያያዘ ለሚገጥሙት ችግሮች በክልል ንግድ ቢሮዎችና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አቤቱታ ቢያቀርቡ በአጭር ጊዜ ምላሽ እንደሚያገኙ ዴስክ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

Share this Post