በህገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ ተገኝቶ ከተያዘው የነዳጅ ምርት ሽያጭ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግስት ገቢ ተደርጓል

በህገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ ተገኝቶ ከተያዘው የነዳጅ ምርት ሽያጭ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግስት ገቢ ተደርጓል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገለቦ ጎልቶሞ። አዲስ አበባ 16/08/2016ዓ.ም (ንቀትሚ))ቢሮው የነዳጅ ምርቶች ዲጂታል ሽያጭ አፈፃፀም ያለበት ደረጃንና የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴን በተመለከተ ከዞን አስተዳዳሪዎች ፣የንግድ ፣መንገድና ትራንስፖርት እና ፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎች እንድሁም በክልሉ ያሉ የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል ። አቶ ገለቦ ጎልቶሞ በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ የነዳጅ ምርት ውጤቶችን በዲጂታል መንገድ ብቻ መንግሥት ባስቀመጠው የሪፎርም አሰራር ሽያጭ መካሄድ እንዳለበት በአፅንኦት ተናግረዋል ። አክለውም የነዳጅ ምርት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መሠረትና የጀርባ አጥንት በመሆኑ መንግስት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን በመመደብ የሚያስገባው ምርት ሲሆን በዘርፉ የሚታየውን ህገወጥነትን ለማረም፣የፀረ ኮንትሮባንድ ግብረ ሃይል ተጠናክሮ ህጋዊና አስተማሪ እርምጃ እየወሰደ እንድመራ ማድረግ ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል ። የቢሮ ኃላፊው ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተደረገው የቁጥጥር ስራ በኮንትሮባንድና በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ የነዳጅ ምርት ተይዞ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ተሽጦ ለመንግሥት ገቢ መደረጉን አብራርተዋል ። መድረኩ ግልፀኝነትን ለመፍጠርና በቀጣይ የማያዳግም እርምጃ ወስዶ ለማረም በቢሮ የተያዘውን አቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ለማድረግ የተዘጋጀ መድረክ ነው ብለዋል። የነዳጅ ምርቶች የዲጅታል ሽያጭና በኤሌክትሮኒክስ የገንዘብ መክፈያ መንገዶች ስርዓት ምንነት ፣ ጠቀሜታ እና የባለፉት ጊዚያት አፈፃፀም ጉድለቶች የሚታረሙበት መንገዶች ላይ በአቶ ካሳሁን ለማ የንግድ የኢንስፔክሽን ሬጉሌሽን ዳይሬክቶሬት ተወካይ አማካኝነት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ። በመድረኩ የቢሮ አመራሮችና የማኔጅመንት አባላት፣ የዞን አስተዳዳሪዎች እና ለሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል። በመድረኩ የተገኙ አካላት መድረኩ የማነቃቂያ ደወል መሆኑን አንስተው የድርሻቸውን በመወጣት ለተያዘው ዓላማ ስኬት እንደሚረባረቡ ቃል ገብተዋል ። በዘርፉ የሚስተዋሉ ማጭበርበር ፣ ከታሪፍ በላይ መሸጥ ፣ የካሽ ሽያጭ፣ ምርት እያለ እጥረት ያለበት በማስመሰል ህብረተሰብን ማወክና ህገወጥ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ፣ ካለው ምርትና አገልግሎት ጋር የማይጣጣም ትስስር መፍጠር ፣ የመጣው ምርት በምን አይነት መንገድ አገልግሎት ላይ እንደዋለ ያለመከታተል። ምርትን በጊዜ አዞ ያለማስመጣት ችግሮችን በቅንጅት መፍታትና የዲጂታል ሽያጭ በማያካሂዱ ማደያዎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ ማረም ከነገ ጀምሮ የሚተገበርና በቀጣይ የ100 ቀናት ዕቅድ አካል ተደርጎ የሚሰራ እንደሆነ አቅጣጫ ተቀምጧል ።

Share this Post