ለኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር መፋጠን የ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ነጋዴዎች መረጃ በዲጂታል ቋት ተደራጅቷል

ለኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር መፋጠን የ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ነጋዴዎች መረጃ በዲጂታል ቋት ተደራጅቷል =================== አዲስ አበባ 19/09/2016(ንቀትሚ) ለኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር መፋጠን እስካሁን የ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ነጋዴዎች መረጃ በዲጂታል ቋት መደራጀቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ። ኢትዮጵያ በ2025 ሀገራዊ አቅሞችን በመጠቀም ፈጠራ የታከለበትና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ዲጂታል ኢኮኖሚ መገንባት የሚያስችል ስትራቴጂ ቀርፃ እየተገበረች ነው። ስትራቴጂው ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ፣ የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ የግልና የመንግሥትን ዘርፎች በማስተሳሰር የዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞን ለማሳለጥ ከሚተገበርባቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ የንግዱ መስክ መሆኑን ገልፀዋል። የዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራ የንግዱን ዘርፍ የዲጂታል ሽግግሩ ዋና ባለቤት ለማድረግ ምቹ ምህዳር እየተፈጠረ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ለዚህም ለረዥም ዓመታት ሲያገለግል የቆየው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ከሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ጋር ተቃኝቶ መሻሻሉን ተናግረዋል። የንግዱ ማኅበረሰብ የንግድ ፈቃድ ምዝገባን ጨምሮ 16 አገልግሎቶችን በበይነ-መረብ አማካኝነት ባለበት ሆኖ በተቀላጠፈ መልኩ የሚገለገልበት የዲጂታል ቋት ተገንብቶ ወደ ሥራ መግባቱን አክለዋል። ኢትዮጵያም በዲጂታል ዘርፉ በዓለም ተወዳዳሪና ተጠቃሚ ለመሆን የኢ-ኮሜርስ ረቂቅ ስትራቴጂ ማዘጋጀቷን ጠቅሰው፤ በቅርቡ ጸድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባም ጠቁመዋል። የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሀገራዊ የዲጂታል ሽግግሩን ለማፋጠን በተሰጠው ተልዕኮ መሠረት የ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ነጋዴዎችን መረጃ ወደ ዲጂታል ማህደር መመዝገቡን ተናግረዋል። ይህንን ግዙፍ መረጃ ደኅንነቱ በተጠበቀ መልኩ በማከማቸትና በመተንተን ለሀገር ጥቅም ለማዋል በኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ የተገነቡ የዳታ ማዕከላት ሚና ጉልህ ስለመሆኑም አንስተዋል። ፓርኩ በርካታ ወጣቶች ሥራ የሚያገኙበት እና የቢዝነስ ሽግግር አድርገው ኩባንያ የሚፈጥሩበት ማዕከል በመሆኑ ከንግዱ ዘርፍ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው ብለዋል። የንግዱን ዘርፍ ዲጂታል ሽግግርን ከማፋጠን አኳያ የባለሙያዎችና የኅብረተሰቡን የዲጂታል ክህሎት ማሳደግ ላይ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል። የኔትዎርክ ትስስር መቆራረጥ ሲያጋጥምም ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር እየተሠራ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል ሲል ኢዚአ ዘግቧል ።

Share this Post