ከ20ሺህ ኩንታል በላይ የእህል ምርት በህገ-ወጥ መንገድ አከማችተው የተገኙ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተወሰደባቸው

ከ20ሺህ ኩንታል በላይ የእህል ምርት በህገ-ወጥ መንገድ አከማችተው የተገኙ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተወሰደባቸው ==================== አዲስ አበባ 28/06/2016ዓ.ም (የንቀትሚ) የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የምግብ ምርቶች በሚደብቁ ወይም በሚያከማቹና ዋጋ በሚያንሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የኢንስፔክሽን ቡድን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በክልሉ በሚገኙ መዋቅሮች ውስጥ ባሉ የንግድ ድርጅቶች ላይ ባደረገው ፍተሻ ከ20ሺህ ኩንታል በላይ የእህል ምርት በህገ-ወጥ መንገድ ተከማችቶ ተገኝቷል፡፡ በህገ-ወጥ መንገድ ተከማችተው ከተገኙት ምርቶ መሀል ጤፍ፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ቦለቄ እና ሌሎችም የእህል ምርቶች ይገኙበታል፡፡ በዚህ ህገ-ወጥ ተግባር የተሰማሩ የንግድ ድርጅቶች በሙሉ የንግድና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያው በሚፈቅደው መሰረት ህጋዊና አስተዳደራዊ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል። ቢሮው ዋና ዋና የሆኑ የግብርና ምርቶችን በመደበቅ፣ በመከዘን ወይም ያለአግባብ በማከማቸት ገበያዉ እንዲራብ በማድረግ የዋጋ ንረት እንዲከሰት እያደረጉ ያሉ አካላት ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ እንደ ጥፋታቸዉ ዓይነትና ደረጃ በንግድ ውድድርና ሸማች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2013 መሰረት ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል ይገልጻል፡፡ በህገ-ወጥ የንግድ ድርጅቶች ላይ ህግ-የማስከበር ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ህገ-ወጥነትን ለመቆጣጠርና ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ቢሮው አሳስቧል። ምንጭ :- ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገብያ ልማት ቢሮ

Share this Post