የግብርና ምርት ውል አዋጅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረክታል።

የግብርና ምርት ውል አዋጅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረክታል። ======================= አዲስ አበባ 12/05/ 2016 ዓ.ም(ንቀትሚ) የግብርና ምርት አምራችና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1289/2015 አንቀጽ 26 ንዑስ አንቀጽ 2 ለግብርና ሚኒስቴር በተሰጠው ስልጣን መሰረት የግብርና ምርት ውል አዋጅን ለማስፈጸም 5 ክፍሎች ያሉት መመሪያ ማዘጋጀት ተችሏል። ይህንንም የግብርና ምርት ውል አዋጅ ለማስፈጸምና ስራውን ወደ መሬት ለማውረድ በተዘጋጀው መመሪያ ላይ የባለድርሻ አካላት ውይይት ተካሂዷል። የውይይቱም ዋና ዓላማ በመመሪያው ላይ የባለድርሻ አካላትን አስተያየት በመሰብሰብ ማስተካከያ ለማድረግ ነው። በውይይቱም ላይ የግብርና ሚኒስቴር፣ የንግድና ቀጠናዊ ትሥሥር እንዲሁም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችና ስራ አስፈጻሚዎች ተገኝተዋል። የግብርና ሚኒስትሩ ዶ/ር ግርማ አመንቴ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት የግብርና ምርት ውል ገበያ ተኮር የሆነ የግብርና ልማት ስራ ለማከናወን በተጨማሪም ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን በስፋት ለማምረት ዕድል ይፈጥራል ብለዋል። የአርሶ አደሩን የተበጣጠሰ መሬት በኩታ-ገጠም በማቀናጀት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የግብርና ምርት አምራችና አስመራች ውል ትልቅ አስተዋጽዖ አለው ሲሉ የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስትሩ ገ/መስቀል ጫላ ተናግረዋል። የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላቸው በግብርና ምርት ውል አዋጅ ልናሳካው የምንፈልገውን ምርታማነትን ማሳደግ በግብዓት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ እና የግብይት ሰንሰለቱን ለማሳደግ በሚፈጥረው ዕድል መሰረት የአዋጁን ማስፈጸሚያ መመሪያ በግልጽ ማስቀመጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። በውይይቱ ላይ የግብርና ምርት ውል አዋጁን ለማስፈጸም የተዘጋጀው መመሪያ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በመመሪያው ላይም የተቋማት ሚናን በግልጽ በማስቀመጥ እንዲሁም መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች በማስተካከል ከወጣው አዋጅ ጋር ማጣጣም እንደሚያስፈልግ በውይይቱ መነሳቱን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኝነው መረጃ ያመለክታል ።

Share this Post