ኢ-ኮሜርስ የሀገር ውስጥ ንግድ እንዲሳለጥ እና ስራ ፈጣሪዎች እንዲበረታቱ ያደርጋል:- አቶ ገብረመስቀል ጫላ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር
===================
አዲስ አበባ 21/08/2016ዓ.ም (ንቀትሚ) ኢ-ኮሜርስ የንግድ ተቋማት ጊዜና ቦታ ሳይገድባቸው ከተጠቃሚዎች ጋር በኦንላይን እንዲገናኙ በማድረግ የሀገር ውስጥ ንግድ እንዲሳለጥ እና የስራ ፈጣሪዎች በሁሉም ስፍራ እንዲበረታቱ እንደሚያደርግ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ብሔራዊ የኢ-ሞኬርስ ስትራቴጅን ለመንግስት አካላት፣ ለግሉ ዘርፍ እና ለባለድርሻዎች ለውይይት አቅርቧል፡፡
ስትራቴጂው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጅን፣ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ የተነደፈ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ኢ-ኮሜርስን በመጠቀም የሀገር ውስጥ ግብይቶችን ማዘመን፣ የወጪ ንግድን ማመቻች እና ጠንካራ የኢኮሜርስ ሎጂስቲክስ ሥርኣት እንዲፈጠር ማድረግ የስትራቴጂው ዋና ዓላማ ነው ያሉት ሚኒስትሩ እንደ ሀገር ልንከተላቸው የሚገቡ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮችን ለይቶ በማስቀመጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተቀናጀ እና አዋጭ በሆነ መልኩ የሚተገብሩባቸውን ስርዓት እንደሚያመላክትም አስረድተዋል፡፡
ዛሬ በተደረገው ውይይት ይበልጥ ዳብሮ እና የሁሉንም ዘርፍ ፍላጎት በማካተት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችል ስታራቴጅ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።