መንግስት የንግድ ዘርፉ ፍትሃዊ፣ ተደራሽና በውድድር ላይ የተመሠረተ ለማድረግ ከምን ጊዜውም በላይ ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ ይገኛል፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ ነሀሴ 23 ቀን 2016 ዓ.ም (ንቀትሚ) መንግስት የንግድ ዘርፉ ፍትሃዊ፣ ተደራሽና በውድድር ላይ የተመሠረተ ለማድረግ ከምን ጊዜውም በላይ ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ ይገኛል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
“የኢትዮጵያን ይግዙ” የንግድ ሳምንት የማጠቃለያ የእውቅና እና ሽልማት መርሃ ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ አምባሳደሮች፣ ሚኒስትሮችና የንግዱ ማህበረሰብ ተሳታፎዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መንግስት የግሉን ዘርፍ የሀገራችን ኢኮኖሚ መሪና አንቀሳቃሽ ለማድረግ የተለያዮ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እየተገበረ እንደሚገኝ ገልፀው ይህን ተከትሎ በንግዱ ዘርፍ በርካታ የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
በ2016 በጀት አመት ከአጠቃላይ ወጪ ንግድ 3.8 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ስኬት ውስጥ የላቀ አስተዋፅኦ ላደረጉ ላኪዎችና ከፍተኛ ተቀባይ ሃገራት ዕውቅና መሰጠቱ የበለጠ መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑን ገልፀው የእውቅና መድረኩ በጋራ ለምናደርገው የብልፅግና ጉዞ አጋዥ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በወጪ ንግድ ዘርፍ የተሠማሩ ላኪዎች በስነ ምግባር በመታነፅ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
በሀገራችን ብልፅግናን ለማረጋገጥ በምናደርገው እልህ አስጨራሽ ርብርብ ውስጥ ከመንግስት ጎን በመቆም አጋርነታችሁን ላሳዮ ባለሃብቶች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡