በእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ስርዓት ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሄደ::

በእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ስርዓት ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሄደ:: ==================== አዲስ አበባ 05/09/2016ዓ.ም (ንቀትሚ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ስርዓት አዋጅ ቁጥር 372/1996 መሰረት ያዘጋጀውን ረቂቅ ደንብ ለባለድርሻ አካለት አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በዚህ አዋጅ የማካኝነት የእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ስርዓት የሙከራ ትግበራ ሲከናወን ቢቆይም በሚፈለገው ደረጃ ተፈጻሚ መሆን ባለመቻሉ ደንቡ መዘጋጀቱን በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የወጪ ንግድ ፕሮሞሽንና ግብይት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ሊቁ በነበሩ ተናግረዋል፡፡ በሙከራ ትግበራው ወቅት በተለይ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ጉዳይ ከፍተኛ ውስንነት ታይቶበታል ያሉት አቶ ሊቁ ይህንን እና ሌሎች የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሁም ተቋማዊ ቅንጅትን፣ የተናጠል እና የጋራ ሀላፊነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ረቂቅ ደንቡን አዘጋጅቶ የሚመለከታቸዉ አካላት አስተያትና ግብአት እንዲሰጡበት ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡ ደንቡን ማዘጋጀት ያስፈለገው የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዐትን ተግባራዊ ለማድረግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 372/1996 ወደ ተሟላ አፈጻጸም የሚያሸጋግር ዝርዝር የአሠራር ሥርዓት ለመፍጠር ሲሆን ዓላማውም ዘመናዊ፣ ግልጽና ወጥ የግብርና ምርቶች የጥራት ደረጃ አወሳሰን አሠራር መዘርጋት፤ በማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት ድርሻ ያላቸውን አካላት ሚና መለየትና በቅንጅት የሚሠሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዲሁም የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲቻል ነው፡፡ በወይይቱ ላይ የተሳተፉ ባለድርሻዎችም የደንቡን መዘጋጀት አድንቀው ቢታከሉበት ይበልጥ ውጤታማ ያደርጉታል ያሏቸውን ጉዳዮችም ጠቁመዋል።

Share this Post