ወደ ሀገር የሚገቡ ምርቶች ተስማሚና ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ አዋጁ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ቋሚ ኮሚቴው አስታወቀ

ወደ ሀገር የሚገቡ ምርቶች ተስማሚና ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ አዋጁ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ቋሚ ኮሚቴው አስታወቀ ====================== አዲስ አበባ 09/10/ 2016 ዓ.ም(የንቀትሚ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ወደ ሀገር የሚገቡ ምርቶች ተስማሚና ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ አዋጁ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አስታወቀ። የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አሻ ያህያ ረቂቅ አዋጁ ከመጽደቁ በፊት በተቋማት መካከል የስልጣን መደራረብ እንዳይፈጠርና የጥቅም ግጭት እንዳይከሰት መድረኮችን በማዘጋጀት እና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የተለያዩ ግብአቶች መሰብሰብ መቻሉን እንዲሁም ረቂቅ አዋጁ ከዚህ በፊት ከነበሩ አዋጆች ጋር እንዳይጣረስ የመፈተሽና የመመርመር ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡ አስገዳጅ ምርቶችን የመቆጣጠርና የመከታተል እንዲሁም ከዚህ በፊት ቅጣት መጣል የማይቻልበት ደረጀ እንደነበር ሰብሳቢዋ አስታውሰው፤ የጥራት ጉዳይ ለሀገራዊ እድገት ካለው ትልቅ ፋይዳ አኳያም ትኩረት የሚሰጠው ነው ብለዋል፡፡ ወደ ሀገራችን የሚገቡ ምርቶች ተስማሚና ደረጃቸውን የጠበቁና ካልሆነ አስቸጋሪ ስለሚሆን ይህንን የሚያስቀር እና ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ጠንካራ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ቋሚ ኮሚቴው መገንዘቡንም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል። ሰብሳቢዋ አያይዘውም ሀገራችን የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠና አባል እንደመሆኗ መጠን ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግና የህግ ማዕቀፉም ትልልቅ ንግድና ሸቀጦች ላይ እየደረሰ ያለውን ማጭበርበር ለመከታተልና ችግሮችን ለመቅረፍ ስለሚያስችል መፅደቅ አለበት ብለን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረ መስቀል ጫላ የመድረኩ ዓለማ አስተያየትና ግብዓት ለመሰብሰብ እንደሆነና ግብዓቱም አዋጁ ከመፅደቁ በፊት የተሻለ አዋጅ ሆኖ እንዲፀድቅ ያግዛል ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ አክለውም የአዋጁ አስፈላጊነት በምርትና አገልግሎት በኢኮኖሚ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሆነ ተናግረው፤ አዋጁን ተከትሎ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እንደሚወጣም ተናግረዋል፡፡ ከኮንስትራክሽን፣ ከምግብና መድሃኒት እንዲሁም ከግብርና ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች ጋር የስልጣን መደራረብ እንዳይኖር ቢፈተሽ ተብሎ ከባለ ድርሻ አካላት የተነሳውን ጥያቄና አስተያየት እንደ ግብዓት ወስደን እንዴት ተመጋግቦ መስራት እንዳለበት በትኩረት ይታያል ሲሉ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ምንጭ :- ዜና ፖርላማ

Share this Post