ኢትዮጽያ በአለም አቀፍ የንግድ አውድ ላይ ተጠቃሚ መሆን የሚያስችላት እምቅ አቅም እንዳላት ተገለፀ።
አዲስ አበባ ነሀሴ 21/2016 (ንቀትሚ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር “የኢትዮጽያን ይግዙ” የንግድ ሣምንት ትኩረቱን በወጪ ንግድ፣ የአለም አቀፍ ንግድ ትስስሮች እንዲሁም ዘርፋን ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሁለተኛ ቀን የፓናል ውይይት አካሂዷል፡፡
በፓናል ውይይቱ ኢትዮጽያ በአለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን የማምረት እና በወጪ ንግድ ዘርፋ ተጠቃሚ መሆን የሚያስችላት እምቅ አቅም እንዳላት ተገልጿል።
በፓናል ውይይቱ የተሳተፋት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ረዳት ኘሮፌሰር ዶ/ር አንዱአለም ጎሹ በሀገራችን ከ60 በመቶ በላይ መታረስ የሚችል መሬት መኖሩን ገልፀው ነገር ግን አሁን ላይ 14 በመቶ ላይ ብቻ እየተመረተ መሆኑን አስረድተዋል።
ረዳት ኘሮፌሰሩ አያይዘውም ሀገራችን በአለም አቀፍ ገበያ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል እምቅ አቅም እንዳላት ገልፀው ይህን አቅም አሟጦ መጠቀም ተገቢ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ሌላው አወያይ አቶ ኤዳኦ አብዲ የኢትዮጽያ የጥራጥሬ የቅባት እህል ላኪዎች ማህበር ኘሬዝዳንት በበኩላቸው የኢትዮጽያ ምርቶች በአለም አቀፍ ገበያ ተመራጭ መሆናቸውን ገልፀው የሀገራችንን ምርቶቾ በአለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አመቺ የሆነ የመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ እንዳለ ተናግረዋል።
የወጪ ንግድ ዘርፋን ለማሳደግ ምርትና ምርታማነት መጨመር፣ የአለም አቀፍ ገበያውን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ምርትን በጥራት ማምረት፣ አሰራሮችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ እና እሴት መጨመር ላይ ማተኮር ተገቢ እንደሆነ ተገልጿል።
በወጪ ንግድ ዘርፋ የፋይናንስ አቅም እና የቴክኖሎጂ ውስንነት በዘርፋ የሚስተዋሉ ችግሮች እንደሆኑ በፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች ተነስቷል።