በንግድ ሳምንቱ የማጠቃለያ መድረክ የተሻለ የውጪ ምንዛሬ ያስገኙ ላኪዎች እውቅና ተሰጣቸው፡፡

በንግድ ሳምንቱ የማጠቃለያ መድረክ የተሻለ የውጪ ምንዛሬ ያስገኙ ላኪዎች እውቅና ተሰጣቸው፡፡ ===================== አዲስ አበባ ነሐሴ 23/2016 ዓ.ም (ንቀትሚ) በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በተዘጋጀው የኢትዮጵያን ይግዙ የንግድ ሳምንት ባዘርና ኤግዚቪሽን የተለያዩ ምርቶችን በመላክ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ያስገኙ ላኪዎች እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ዘርፍ የተሰማሩና በዘርፉ በትኩረት በመስራት ወደ ተለያዩ መዳረሻ ሀገራት ምርቶችን በመላክ የተሻለ የውጪ ምንዛሬ ያስገኙ ነጋዴዎች በተሰማሩባቸው ዘርፍች ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እጅ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባዘጋጀው የእውቅና ፕሮግራም ማዕድን፣ፍራፍሬ፣ቁም እንስሳት፣የቆዳ ውጤቶችን በመላክ፣የእንስሳት መኖ አትክትልት፣ስጋና ወተት፣ምግብና መጠጥ፣ጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ጫት፣ የቅባት እህሎች፣ጥራጥሬ አበባና እና ቡና በመላክ የተሻለ የውጪ ምንዛሬ ለሀገራችን ያስገኙ ላኪዎች የምስጋና የምስክር ወረቀትና የዋንጫ ሽልማት ከአቶ ተመስገን እጅ ተቀብለዋል፡፡ በየተሰማሩበት የወጪ ንግድ ዘርፍ ባስገኙት የውጪ ምንዛሬ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የወጡ ላኪዎች እውቅናና ዋንጫ ሲበረከትላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሁሉም ዘርፎች የተሻለ ምንዛሬ በማስገኘት ራሳቸውንና ሀገራቸውን የጠቀሙት አብዱልሀኪም መሀመድ ገለቶ፣ሸር ኢትዮጵያ እና ትራኮን ትሬድንግ የአሸናፊዎች አሸናፊ በመሆን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ ዋንጫ ተረክበዋል፡፡ ሶስቱ ላኪዎች በድምሩ 313.68 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለሀገራችን አስገኝተዋል፡፡

Share this Post