የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በየክልል ከተሞች ህገ ወጥ የንግድ ተግባራትን የፈፀሙ 1,671 የንግድ ድርጅቶች የታሸጉ መሆኑን አስታወ፡፡
=========================================
አዲስ አበባ ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም (ንቀትሚ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ከብሄራዊ የንግድ ተቋማት የፀረ ህገ ወጥ ንግድና ገበያ መቆጣጠረያ የጋራ ኮሚቴ ጋር ባደረጉት ግምገማ በየክልል ከተሞች ህገ ወጥ የንግድ ተግባራትን የፈፀሙ 1,671 የንግድ ድርጅቶች የታሸጉ መሆኑን አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሩ አያይዘውም ከዚህ ቀደም በሰሩት ህገ ወጥ የንግድ ተግባራት ምክንያት ታሽገው የነበሩ 18,789 ድርጅቶች የውል ስምምነት እንዲፈፅሙ እየተደረገ እሸጋው ተነስቶላቸው ወደ ስራ የተመለሱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል በዛሬው እለት የታሰሩትን 82 ነጋዴዎች ጨምሮ እስካሁን በድምሩ 628 ነጋዴዎች የታሰሩ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 182 ነጋዴዎች ከእስራት የተፈቱ መሆኑን ሚንስትሩ አስታውቀዋል፡፡
ዶ/ር ካሳሁን እንደገፁት እየተደረገ ባለው ክትትልና ቁጥጥር በዛሬው እለት ብቻ በግንባታ እቃዎች ላይ ህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 21 የሲሚንቶ፤7 የብረት፤10 የቆርቆሮ፤ 3 የሚስማር እና 2 የሴራሚክ የንግድ ተቋማት ታሽገዋል፡፡
በየጊዜው በተደረጉ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በምግብ ዘይት፣ በዱቄት፣ ስኳር፣ ቲማቲም፣ ድንችና በመሳሰሉት ምርቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ የታየባቸው መሆኑንና ገበያ የማረጋጋት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በቀጣይ ቀናት በጤፍ፣ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ፓስታ፣ መካሮኒ እና ጥራጥሬ ምርቶች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ ዶ/ር ካሳሁን አስታውቀዋል፡፡