በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ከ330 በላይ የእሁድ ገበያን በማስፋፋት የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እንዲደርስ ተደርጓል
አዲስ አበባ 05/09/2016ዓ.ም(ንቀትሚ) በኦሮሚያ ክልል ከ330 በላይ በሚሆኑ ከተሞች ላይ የእሁድ ገበያ አገልግሎት በማስፋፋት የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እንዲደርስ መደረጉን የክልሉ ንግድ ቢሮ ገለፀ።
የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ መሰረት አሰፋ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በውስን የክልሉ ከተሞች ላይ የነበረው የእሁድ ገበያ አገልግሎትን ከ330 በላይ ከተሞች በማድረስ የዋጋ ንረትን መቆጣጠርና የገበያ መረጋጋት እንዲኖር ሰርቷል።
ባለፉት አስር ወራት ብቻ ከ200 በላይ የሚሆኑ የእሁድ ገበያ ቦታዎች መከፈታቸውን የገለጹት ሃላፊዋ በዚህም የግብርና ምርቶች በተለይ ጤፍ፣ የዳቦ ዱቄት፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም እንቁላልና የእንስሳት ተዋጽኦ ላይ የገበያ መረጋጋት መፈጠሩን ተናግረዋል።
በተለይም የሽንኩርትና የቲማቲም ዋጋ ቅናሽ ማሳየቱን ጠቅሰው በተመሳሳይ የጤፍ ዋጋ ላይም ቅናሽ መታየቱን አስረድተዋል።
ቅናሹ የታየው የእሁድ ገበያን ከማስፋፋት ባለፈ ሕገ ወጥነትን በመከላከልና ምርቱ በቀጥታ ሸማቹ ዘንድ እንዲደርስ በመደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ህገ ወጥነትን ለመከላከል በተደረገው ጥረት ከ69 ሺህ በላይ የሚሆኑ የንግድ ሱቆች ላይ ከማሸግ ጀምሮ የንግድ ፍቃድ መሰረዝና የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱንም ጨምረው ተናግረዋል ።
በተለይ በከተሞች አካባቢ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ወተት፣ እንቁላልና ሌሎች የፍጆታ እቃዎችና የግብርና ምርቶችን በቅናሽ ለሸማቹ በማቅረብ ላይ የተሻለ ስራ መሰራቱን አመልክተዋል።
በቢሮው የሬጉላቶሪ ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ገሾ፣ በበኩላቸው የንግድ አሰራር ስርዓትን ዲጂታላይዝ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ሕግ የወጣላቸው ምርቶች በዲጂታል ግብይት ብቻ እንዲከናወኑ፣ የንግድ ፍቃድ ምዝገባና እድሳት በዲጂታል እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ሆነው ከተፈለገው ዓላማ ውጭ የተንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይም የንግድ ፍቃድ በመንጠቅ እርምጃ መወሰዱንም አመልክተዋል።
በሸማቾች ጥበቃ መብት ላይ ማህበረሰቡ ተገቢውን ክህሎትና ዕውቀት እንዲኖረው 41 በሚሆኑ ከተሞችና ዞኖች ላይ ቦርድ ተቋቁሞ የትምህርትና ግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም የንግዱን ማህበረሰብ ግዴታና የሸማቾች መብትና ጥቅም ላይ የጋራ አረዳድ እንዲኖር እየተሰራ ነው ብለዋል ሲል የዘገበው ኢዚአ ነው።